

የግብርና ሚኒስቴር፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የአብክመ ግብርና ቢሮ ከኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለቀበሌ ልማት ጣቢያ ሰራተኞች የደረጃ ሶስትና የደረጃ አራት የደረጃ ማሻሻያ የክህሎት ልማት ስልጠና ማስጀመሪያ መርሀግብር አካሂዷል።
በፕሮግራሙ የፌደራል ግብርና ሚኒስቴር ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የአብክመ ግብርና ቢሮ ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች፣ የአብክመ እንስሳት ተዋጽኦና መኖ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር፣ የግብርና ኮሌጆች ክትትል ባለሙያ፣ የአብክመ እንስሳት ሀብት ልማት ኤክስቴንሽን ባለሙያ፣ ከአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ኤክስቴንሸን ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር፣ የኮሌጁ አመራሮች፣ መምህራኖች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና ሰልጣኞች በተገኙበት ስልጠናዉ መጀመሩን አብስረዋል።
የኮሌጁ ዲን አቶ በዛብህ ይመር በመክፈቻ ንግግራቸዉ የነገዉን የግብርና ትራንስፎርሜሽን እዉን ለማድረግ ዛሬ ሁላችንም በጋራ መቆም ይኖርብናል ብለዋል።
የዚህ ስልጠና አላማ የአርሶአደሩን የቴክኖሎጂ ፍላጎት፣ እዉቀትና ክህሎት ከቀበሌ ባለሙያዎች ጋር ለማጣጣምና የባለሙያዎቹን ደረጃ ማሻሻልና ከፍ ማድረግ ነዉ ያሉት ከፌደራል ግብርና ሚኒስቴር አቶ ላቃቸዉ ልመንህ ተማሪዎች በኮሌጅ ቆይታቸዉ ህግና ደንብን በማክበር ስልጠናዉን በአግባቡ እንዲከታተሉ አደራ ብለዋል።
በግብርናዉ ዘርፍ እያደገ የመጣዉን ቴክኖሎጂና አዲስ አሰራር በወቅቱ በመተዋወቅ ለአርሶ አደሩና ለተጠቃሚዉ ማህበረሰብ እዉቀትና ክህሎቱን ለማሳደግ ለአርሶ አደሩ የሚሰጠዉን የግብርና ኤክስቴንሽን ጥራት እንዲኖረዉ ለማድረግ ስልጠናው አስፈላጊ ነዉ ያሉት የአብክመ ግብርና ቢሮ ኤክስቴንሽን ኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተመስገን ምህረቱ ናቸዉ።
ከስልጠናዉ ባሻገር ሰልጣኞች በኮሌጅ ቆይታቸዉ መብትና ግዴታቸዉን አዉቀዉ በአግባቡ ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉና አጠቃላይ የስልጠና ሂደቱን የኮሌጁ አካዳሚክ ዲንና የኮሌጁ ተማሪዎች አገልግሎት ኦረንቴሽን ሰጥተዋል።
ስልጠናዉ ለተከታታይ 6ወራት የሚቆይ ሲሆን መርሀግብሩም ከሰልጣኝ ተማሪዎች ጋር በስልጠናዉ ዙሪያ አጠር ያለ ዉይይት በማድረግ ተጠናቋል።
ኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ህዝብ ግንኙነት
ኮ/ ግ /ኮ መጋቢት 26/2018 ዓ.ም