የኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመቀናጀት የፌደራል ከፍተኛ አመራሮችን ከኮምቦልቻ አየር ማረፊያ ጀምሮ ደማቅ አቀባበል ያደረገ ሲሆን በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ የቀበሌ ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን ከደረጃ 3 ወደ ደረጃ 4 ማሻሻያ ስልጠና ለማስጀመር የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ፣ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የፌደራል ከፍተኛ አመራሮች፣ የክልል ከፍተኛ አመራሮች ፣የስራ ክፍል ሃላፊዎችና አጋር የስራ አካላት በተገኙበት በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ በዛሬው እለት በይፋ አስጀምሯል።
ለመጀመሪያ ዙር የተመረጡ የቀበሌ ልማት ጣቢያ ሰራተኞች የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና መጀመሩን ያበሰሩት የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ የስልጠናውን ቀጣይነትና ስልጠናው በተለያዩ ዙሮች የሚሰጥ መሆኑን ስልጠናውን ለመስጠት በተዘጋጀው የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ አሳውቀዋል።
የደረጃ ማሻሻያ ስልጠናው ቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል፣ ግብርናን ድጅታላዝድ በማድረግ አርሶ አደሩ የአንድ ማዕከል መረጃ የማግኘት ስራ መጀመሩ እና አርሶ አደሩ የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኝ አየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዶ/ር ግርማ አመንቴ ገልጸዋል፡፡ ሚኒስተሩ አክለውም ስልጠናው የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎት በማሻሻል ለምርትና ምርታማነት፣ ለእድገትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ድርሻው የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ በዞን የሚገኙ የቀበሌ ልማት ጣቢያ ባለሙያዎችን የእውቀትና ክህሎት ደረጃ ለማሻሻል የሚሰጠውን የደረጃ 4 ማሻሻያ ስልጠና የግብርና ልማት ጣቢያ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ውጤታማ ለማድረግ በመመልመያው መስፈርት መሰረት የደረጃ ማሻሻያ ስልጠና ለመዉሰድ በኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ መግባታቸውን በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ድረስ ሳህሉ ገልፀዋል።
አያይዘውም የግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞች የረጅም ጊዜ ጥያቄ መልስ ማግኘቱን እና በቀጣይም ለግብርና ልማት ጣቢያ ሰራተኞች ተከታታይ ስልጠና የሚሰጥ መሆኑን ዶ/ር ድረስ በመክፈቻ ንግግራቸው አሳውቀዋል።
የደረጃ ማሻሻያ ስልጠናው ከደረጃ 4 በታች ያሉ የቀበሌ ግብርና ባለሙያዎችን በየትምህርት ዘርፉ በግብርና ኮሌጆች በማስገባት እና በማሰልጠን ብቁና ተወዳዳሪ ለማድረግ ፣ለምርትና ምርታማነት እድገት፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ ፣ ድርሻው የጎላ መሆኑን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገልጸዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትሯ አክለውም ስልጠናው የቀበሌ ልማት ጣቢያ ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎት በማሻሻል ለምርትና ምርታማነት እድገትና ለስራ ዕድል ፈጠራ ድርሻው የጎላ መሆኑን፣ ለቀጣይ ከግብርና ሚኒስትር ጋር በመቀናጀት ስልጠናው እንደሚሰጥና ቀጣይነትም እንደሚኖረው ገልጸው ባለፉት አመታት በግብርናው ዘርፍ የመጡትን ለውጦች በተባበረ ክንድ ልናስቀጥል ይገባል ሲሉ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ተናግረዋል።
የዝግጅቱ የመጨረሻ መርሃ ግብር የሆነው የጋራ የፎቶግራፍ ዝግጅትና በኮሌጁ ቅጥር ግቢ የሚገኙ ቤተ መጻህፍት እና የተማሪዎች የመማሪያ ላብራቶሪ ክፍሎችን በመጎብኘት የእለቱ ዝግጅት ተጠናቋል።
ኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ ህዝብ ግንኙነት
ኮምቦልቻ ግብርና ኮሌጅ 29/7/2017 ዓ.ም